- Global Voices በአማርኛ - https://am.globalvoices.org -

ይህ የባቡር መሥመር የአቡነ ጴጥሮስንና የዐፄ ምኒሊክን ሐውልት እንዲነሡ ያደርጋል?

Categories: የዜጎች መገናኛ ብዙሐን

ጊዜው 1988 ዓ.ም. ነበር፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን በትዕቢት የወረረችበት፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩት አጼ ምኒልክ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው አሰልፈው የጊዜውን ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ጦር አድዋ ላይ ድል አደረጉ፡፡ በቀሪው የንግስና ዘመናቸው ደግሞ በዘመኑ መንፈስ የተቃኙ ብዙ ስራቸውን ሲያከናወኑ የባቡር መስመርን ጨምሮ በርካታ ስልጣኔዎች ወደሀገራችን እንዲገቡ ጥረት በማድረግ አሳልፈዋል፡፡  ለዚህ  የአድዋ ድልና ሀገሪቱ ዘመናዊ እንድትሆን ላደረጉት ጥረት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ይህ  ሐውልት በመሐል አዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ ቆመላቸው፡፡

 በቆራጥ ኢትየጵያውን ጽናት የተሸነፈው የጣሊያን ጦር ለአራት አስርት ዓመታት ራሱን ሲያደራጅ እና ሲያደባ ቆይቶ  በ1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ወረረ፡፡ ከመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውን ጳጳሳት አንዱ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እጃቸውን ተይዘው ማርሻል ግራዚያኒ ፊት ቀረቡ፡፡ “የኢጣሊያ መንግስት ገዢነትን  አሜን ብለህ ተቀበል” ተብለው ሲጠየቁ “የኢትየጵያ ህዝብ ለዚህ ጠላት እንዳይገዛ አውግዣለው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡በፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተወገዘች ትሁን፡፡” ብለው ተናገሩ፡፡ከዚያ በማርሻል ግራዚያኒ ትእዛዝ በስምንት ጥይት ተደብድበው ወደቁ፡፡ አለመሞታቸው ሲታወቅ ከግራዚያኒ አዛዦች አንዱ በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራሳቸውን በመምታት ገደላቸው፡፡  ይህን ለሀገር ነጻነት የከፈሉትን መስዋዕትነት ለማዘከር በግፍ ከተገደሉበት ቦታ በቅርብ ርቀት ሐውልት ተሰራላቸው፡፡

ይሁንና ከቻይናው ሪልዌይ ግሩፕ ሊሚትድ ጋር በመተባበር  የከተማ ባቡር መስመር ለመዘርጋት ያቀደው  የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ሁለት ሐውልቶች ሊያፈርስ መዘጋጁቱ ብዙ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል፡፡

 ስለኢትዮጵያ ታሪክ ባሕል እምነት ፖለቲካ እና ትውፊት ምልከታውን የሚያቀርበው ዳንኤል ክብረት [1]  መሠረታዊ ጥያቄውን በማስቀድም ትችቱን አስከተለ፡ [2]

 

ይህ የባቡር መሥመር የአቡነ ጴጥሮስንና የዐፄ ምኒሊክን ሐውልት እንዲነሡ ያደርጋል?

ለዚህ ጥያቄ ምላሹ ‹አዎን› ከሆነ ስለ ባቡሩ የሚኖረን ግምት ይለያል፡፡ ኢትዮጵያን እናሳድጋለን ስንል ያሳደጓትን እየዘነጋንና መታሰቢያቸውን እያፈረስን መሆን የለበትም፡፡ ‹በማን ላይ ቆመሽ እግዜርን ታሚያለሽ› አለ ያገሬ ሰው፡፡ የምናመጣው አዲስ ነገር ባለን ላይ የሚጨመር እንጂ ያለንን የሚያጠፋ መሆን የለበትም፡፡ መኪና ያስፈልገናል፣ ግን እግር የሚቆርጥ መሆን የለበትም፡፡ ወደድንም ጠላንም ይህች ሀገር የታሪክና የቅርስ ሀገር ናት፡፡ ይህ ታሪኳና ቅርሷ ደግሞ የህልውናዋም ምንጭና መሰንበቻም ጭምር ነው፡፡ ይህን ታሪክና ቅርስ እያጠፉና እያበላሹ የሚመጣ ለውጥ አንገት ቆርጦ ፀጉርን እንደማስተካከል ነው የሚቆጠረው፡፡ እናም የሚመለከታቸው ሁሉ ወደ ርምጃ ከመግባታቸው በፊት ሦስት ጊዜ ሊያስቡ ይገባል፡፡ መቼም የመጀመርያውን ባቡር ያስገቡትን የዐፄ ምኒሊክን ሐውልት አፍርሶ ባቡር እናስገባ ማለት የታሪክ ምጸት ነው፡፡ ለነጻነት የተሠውትን የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ነቅሎ በባቡር ላይ በነጻነት ለመሄድ መከጀል ግፍ መሥራት ነው የሚሆነው፡፡”

 

አብይ ተክለ ማርያም [3] ደግሞ ይህ ወሬ ውሽት እንዲሆን ተመኝቷል፡፡ [4]

አሁን በአዲስ አበባ እየተገነባ ላለው የባቡር መስመር ዋና ቲፎዞ ነኝ፡፡ ከአራት አመት በፊት ስለእርሱ ረጅም መጣጥፍ ጽፌ ነበር፡፡ ነገር ግን እጅግ ጥልቅ የዐሳብ ድህነት ያጠቃቸው የከተማችን ንድፍ ሰሪዎች መስመሩን ለመዘርጋት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጣቸውን ታላላቅ የታሪክ ምልክቶችን የሚዘክሩ ሁለት ሐውልቶች ለማፍረስ ወይም ቦታቸውን መቀየር አለብን ብለዋል? በፌስቡክ ያነበብካቸው አሉባልታዎች ውሸት እንዲሆኑ ተስፋ አደርጋለው፡፡

 

ሙሴ ጌታቸው ቀጠለ፡፡ [5]

1.ጧት ጉዞ ላይ ሳለሁ፤ ፋና ሬዲዮ ይፈርሳሉ ተብሎ እየተወራ ያለው የአጼ ምኒልክ እና የአቡነ ጴጥሮስ ኅውልቶች የማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚያናፍሱት ያልተጣራ አሉባልታ እንደሆነ ነገረን።

2. ፋና በተጨማሪ እንዳወራው አዲስ አበባ መንገዶች ሊያሰራ ባአቀደው መንገድ፦

1.1. የአቡነ ጴጥሮስ ኅውልት ብቻ ተነስቶ፤ መንገዱ ከተጠናቀቀ በኋላ ተመልሶ እንደሚተከል

1.2. የአጼ ምኒልክ ኅውልት ግን በምንም ምክንያት እንደማይነካ ነበር የነገረን።

3. አሁንም ኢህአዴግ/መንግስት ካለው ድብቅነት ያስተላለፈው መልዕክት በፍፁም አላምነውም። ይህም እንደ ቀድሞዎቹ ጀግኖቻችን እና አርዓያዎቻችን የመግደል አባዜ ነው።

4. የአውሮፓ የጥንት ከተሞች ላይ ያሉ ኅውልቶችም ሆኑ የቅርስ ቦታዎች በመሰረተ ግንባታ ምክንያት ሲፈርሱ ሰምቼም አይቼም አላውቅም። ከዚህ በተቃራኒ Site Adaptation በመጠቀም ከቀድሞ ጎልተው እንዲታዩ ይደረጋሉ።

5. ምናልባት ህዝቡን ለማሳመን መንግስት ይህንንም እንደሌሎቹ ልምዶች (የምርጫ የስነ-ምግባር ህግ፣…) “ከሌሎች አገሮች የቀሰምኩት ምርጥ ልምድ ነው” ማለት ነበረበት።

አንድ አድርገን [6] የተባሉ ህቡዕ ጦማሪያን ደግሞ አስተያየታቸውም [7] እንዲህ አስፍረዋል፡፡

 እኛ እያልን ያለነው ሀገሪቱ ላይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ለምን ቅድመ ጥናት ሲካሄድ የእምነትና የሐውልት ቦታዎች ፤ የአባቶቻችን ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለኢትዮጵያ አሻራቸውን ያስቀመጡበት ቦታ ከግምት ውስጥ አይገባም ? ወይስ ከበስተጀርባ ሌላ ነገር አለ……?..

 

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ [8] በመካነ ድሩ ዜናውን አስተባብሎ እርስ በርሱ የሚጣረስ ዘገባውን አስነብቧል፡፡ [9]

 ሀውልቱ  ምንም ችግር ሳይደርስ የባቡር መስመር ዝርጋታው ይከናወናል ያሉት ሃላፊው ፥ የባቡር መተላለፊያ ዋሻ ከሃውልቱ ስር ስለሚገነባ ፤ ግንባታው እስኪያልቅ ድረስ ሃውልቱ ለጥቂት ጊዜ ተነስቶ ከዋሻው መጠናቀቅ በኋላ ወደ ቦታው እነደሚመለስ ተናግረዋል።አያይዘውም ይህ የባቡር መስመር ግንባታ የዳግማዊ ሚኒሊክ ሀውልትን በምንም መልኩ እንደማይነካው የሚወራው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑንም ነው ያስረዱት።”

 

መንግስት በሐውልቶች ምክንያት ከህዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥመው ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት በቻይና መንግስት በተገነባው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ቅፅር ግቢ ውስጥ የአፍሪካ አባት ተብለው የሚጠሩት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴን በመተው ለጋናዊው ክዋሜ ንክሩማህ መሰራቱ ብዙዎችን እንዳስከፋ [10] የሚታወስ ነው፡፡